ወይዘሮ ወላንሳ

 

...ምነው ልጄ ተላላና ሞኝ አታ'ርገኝ እንጅ፣

ነጋ-ጠባ ከቤቴ ስገባ፣ ስወጣም ከደጅ፤

ኦረ የጊዮርጊስ ያለህ፣ የገብሬል፣ የሚጣቁ!

መች ይጠፋኛል ጠላቴ? እለየዋለሁ እንጂ ከሩቁ፣

አንተ ብቻ ዳዊቱን ዝም ብለህ ድገም፣ በርትተህ ጸልይልኝ፣

ለ'ዚ'ትነ 'መ-ብርሃን አደራ! ብለህ፣ 'ማልደህ ንገርልኝ፣

አታ'ረገውም እንጅ፣ እንደልቤ'ማ ብታ'ረግልኝ፣

ጠላቴን አንድ-ባንድ ይዛ አንገት-አንገቱን ብትቀነጥስልኝ፤

ደስታውንም አልችለው፣ ጨፍሬም አላበቃ፣

እልል! ብዬም አላባራ፣ ጐረሮዬም ቢነቃ።

 

አደራሽን እመቤቴ ጠላቶቼን መቀመቅ ጨምሪልኝ...

የልቤን ዘርዝሬ ነግሬያታለሁ ብትሰማኝ ጸሎቴን፣

ካልሆነም እኔው ራሴ ልቅደም፣ ትስጠኝ ሞቴን!

ካስጨከናት'ማ ልሙት በቃ፣ ታሳጥረው ሕይወቴን።

 

የማንም መጫወቻ ሆንኩ አይደል፣ እኔ ወላንሳ!

በትንሹም፣ በትልቁም የማየው ይኸ ሁሉ አበሳ፣

እኔ አክስትህ መለሳለስ፣ መለማመጥ መቻ'ውቅና!

ጠቅላላ ጠላቴ ተራ-በተራ ሞቶ ይለቅና፣

የመጨረሻዋን ሳንቲምም ብትሆን ፈትቼ መቀነቴን፣

ቆንጆ ጃንጥላ ገዝቼ ለመቤቴ፣ አስገባለሁ ለመምሩ ስለቴን...

እያሉ ሰነበቱና አክስቴ ሲዝናኑብኝ፣ ሲፎክሩ፣ ሲደነፉ፣

አንድ ቀን በማለዳ ጓዛቸውን ይዘው፣ እፍ! ብለው ጠፉ...

                                      ይቀጥላል...

                   

                                     ገ/ኢ. ጐርፉ።